Posted on

​​​​​​​ጤፍ የኢትዮጵያ ፀጋ

ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትጵያውያን በቋሚነት የሚመገቡትን ጤፍ፣  ከምግብነትም ባለፈ ከአምላክ የተሰጠ ፀጋ ነው ብለው ይገልጹታል፡፡

እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ የተሻሻሉና አሁንም ድረስ ምርት ላይ ያሉ 42 ዓይነት የጤፍ ዝርያ ፀጋ ያላት ኢትዮጵያም ጤፍን በየዓመቱ በሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ታበቅላለች፡፡

ጤፍ ለኢትዮጵያውያን ምግባቸው፣ ልማዳቸው፣ ባህላቸውና መገለጫቸውም ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች ሲነሳ ከክትፎው፣ ከቆጮው፣ ከአተካናው፣ ከእልበቱ፣ ከዶሮ ወጡ እንደ ሕዝቡ ብዝኃነት ከሚቀርቡቱ የባህል ምግቦች ሁሉ የጤፍ ልጅ የሆነው እንጀራ በኢትዮጵያ አብዛኞቹ አካባቢዎች ቀድሞ የሚወሳ ነው፡፡ ጤፍ ለኢትዮጵያ ከምግብነትና ባህልም ባለፈ ንግድም፣ መለያም ጭምር ነው፡፡ ብዙዎች ከጥሬ እስከ ዱቄት ብሎም እስከ በሰለው እንጀራ ድረስ በአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከብረውበታል፡፡

ከግሉቲን ነፃ የተባለው ጤፍ ከኢትዮጵያ አልፎ በውጭው ዓለም ከመሪዎች ጓዳም ዘልቋል፡፡ በኢትጵያውያን ዘንድ ጤፍ ለረዥም ዓመታት ለእንጀራ፣ ለቂጣ፣ ለገንፎ፣ ለአነባበሮ፣ ዳጉሳ ጤፍ ከሆነ ለጠላ ሲውል የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ከጤፍ የሚዘጋጁ ምግቦች በርክተዋል፡፡ ከጤፍ ፒዛ፣ ኬክና ዳቦ፣ ፓስታና ብስኩት በውጭው ዓለም ጁስ ሁሉ ሳይቀር ማግኘትም ተለምዷል፡፡

የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ወይዛዝርት ደግሞ ዛሬ ላይ ለውበት መጠበቂያ ሲባል ፊትን በስክራፕ (ከፊት ላይ የሞቱ የቆዳ ሴሎችን ለማስለቀቅ የሚረዳ ቅባት) እንደሚጠቀሙት ሁሉ ጤፍን ከሞቀ ውኃ ጋር በማዋሃድ ፊታቸውንና ገላቸውን በጤፉ በማሸት ውበት ይጠብቁበት ነበርም ይባላል፡፡

ቀይ፣ ነጭ፣ ቡንኝ፣ ሠርገኛ እየተባሉ እንደጤፍ አብቃይ አካባቢዎች የሚጠሩት የጤፍ ዓይነቶች የጤፍ ግብርናን ከ40 ዓመታት በላይ ለዘለቁበት ለአቶ ተስፋዬ መኮንን ዓይነቱ አርሶ አደር፣ ጤፍ ከቤታቸው ሊለዩት የማይፈልጉት የቤተሰብ አባል ያህል ነው፡፡

‹‹ጤፍ ድሮም የኛ ነው፡፡ በልጅነቴ የመሳፍንት ምግብ ነው ሲባል እሰማ ነበር›› ያሉት አርሶ አደር ተስፋዬ፣ መቂ ላይ ጤፍ ማምረት ከጀመሩ ከ30 ዓመት በላይ እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ፡፡

‹‹ጤፍ የራሳችን ነው፡፡ ከአገር ከወጣ ዘሩ ይጠፋብናል እየተባለ ታምሶና ተፈጭቶ ሲላክ አስታውሳለሁ›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ ባላቸው አንድ ቀረጥ (ሩብ ሔክታር) መሬት ጤፍን ማልማት የሙጥኝ ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡ እንደቀድሞው በወጣትነት ዘመናቸው የሚያውቋቸውን ዓይነት የጤፍ ዝርያዎች እየተመናመኑና በተሻሻለ ዝርያ እየተተኩ መሆኑን በመግለጽም አሁን ላይ በአካባቢያቸው ‹‹በዚህ ዘመን የመጣ›› የሚሉትንና የአካባቢው ሰው ‹‹ኪሮሽ›› የሚለውን የጤፍ ዝርያ እንደሚጠቀሙም ይናገራሉ፡፡

አቶ ተስፋዬ ጤፍ የማን ነው ቢሏቸው ‹‹የኛ›› ከማለት ውጭ ሌላ መልስ የላቸውም፡፡ ጤፍ የናንተ አይደለም የኛ ነው የሚል ሌላ አገር ቢመጣስ ሲባሉም ‹‹ይህማ አይሆንም ከአባቶቼ የወረስኩት ነው›› የሚል መልስ አላቸው፡፡

ከዛሬ 14 ዓመት በፊት የጤፍ ባለቤትነት ከኢትዮጵያ አፈትልኮ የሆላንድ ድርጅት ሆኗል ሲባል በግብርናውና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ያሉ ምሁራንና መንግሥትም መተኛትን አልመረጡም ነበር፡፡ በየጊዜውም የጤፍ ባለቤትነት የኢትዮጵያ መሆኑን ለማሳመን ሲወተውቱ ከርመዋል፡፡ ዓመታትን የፈጀው ትግላቸው ፍሬ አልባ ባይሆንም፣ የጤፍ ባለቤትነት የኔ ነው ያለው የኔዘርላንድ ኩባንያ ሔልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል ቢቪ፣ በሆላንድ፣ በኦስትሪያ፣ በእንግሊዝ፣ በቤልጂየምና በጣሊያን ውስጥ የባለቤትነት ፈቃድ አግኝቶ ጤፍን ሲቸበችበው ኖሯል፡፡

ባለቤትነትን ማጣት ምናልባትም በጤፍ እርሻ ለሚተዳደረው አርሶ አደሩ ብሎም ጤፍን መሠረታዊ ምግቡ ላደረገው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያስከተለው ኪሳራ ግልጽ ባይሆንለትም፣ ምሁራኑ ግን ‹‹የተሰጠንን የጤፍ ፀጋ ዘር መልሰን የምንገዛበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፣ መታገል አለብን›› ብለው ነበር የተነሱት፡፡

ኩባንያው ከዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩትና ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር የጤፍ ምርምርን ለመደገፍ፣ ለባለሙያዎች፣ የትምህርት ዕድል ለመስጠት፣ ጤፍ በአውሮፓ ሲዘራ አሥር ዩሮ ለመክፈል ከተጣራ ትርፉም አምስት በመቶ ለመክፈል ውል ገብቶ የጤፍ ዝርያዎችን ወስዶ ነበር፡፡

ሆኖም የታሰበው ሳይሆን ያልታሰበው ሆኖ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ክዶ ለዓመታት ቆይተዋል፡፡ ከአውሮፓ ፓተንት ጽሕፈት ቤት አዲና አያናና ተስፋዬ በተሰኙ የጤፍ ዝርያዎችም ባለቤትነት መብት አግኝቶ ነበር፡፡

ለዓመታት በሆላንዱ ኩባንያ የቆየውን የጤፍ ባለቤትነት መብት ለማስመለስም በኢትዮጵያ መንግሥትም በኩል የተጀመሩ ጥረቶች በተሻለ መጠን ፈር የያዙት በየካቲት 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት፣ ከሳይንስና ኢኖቬሺን ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተው ቡድን የጤፍ ባለቤትነትን መብት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡

የጤፍን ባለቤትነት መብት ለማስመለስ ክስ መመሥረት፣ ዲፕሎማሲያዊ ዕርምጃ መውሰድና ሕዝባዊ ዘመቻ ለማካሄድ ውሳኔ ተላልፎ የነበረ ሲሆን፣ ሰሞኑን ኢትዮጵያ የጤፍ ባለቤት ስለመሆኗ ዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ውሳኔ ማሳለፉ ተሰምቷል፡፡

https://www.ethiopianreporter.com/article/14733

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *